የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና የአቅርቦት ችግሮቹ

Untitled.png

ከጥቂት ቀናት በፊት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትና ፔትሮ ቻይና የአንድ ዓመት የነዳጅ አቅርቦት ስምምነት መፈራረማቸው በብዙ መገናኛ ብዙሃን መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለአንድ ዓመት ፍጆታ የሚውል ነዳጅ ለመግዛት ያወጣውን ዓለም አቀፍ ጨረታ ካሸነፈው ፔትሮ ቻይና ጋር ነው የአቅርቦት ስምምነቱን የተፈራረመው፡፡ በፔትሮ ቻይናና በነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መካከል የግዥ ስምምነቱ በተከናወነበት ወቅት እንደተገለጸው፣ እ.ኤ.አ. ከጃንዋሪ 1 ቀን 2019 እስከ ዲሴምበር 31 ቀን 2019 ድረስ ለአንድ ዓመት የሚውለውን የነዳጅ ፍጆታ ፔትሮ ቻይና በዓለም ዋጋ መሠረት የወርኃዊ አማካዩን በማስላት ያቀርባል፡፡ ለፔትሮ ቻይና የአገልግሎት ክፍያ የሚፈጸመውም ከየአንዳንዱ በርሜል ላይ በሚሰላ ፕሪሚየም ዋጋ መሠረት ይሆናል፡፡ ፔትሮ ቻይና ነዳጁን ወደብ ድረስ በማጓጓዝ ያሸነፈበት ፕሪምየም ዋጋ፣ ለአውሮፕላን ነዳጅ 5.7 ዶላር በበርሜል፣ ለናፍጣ 4.78 ዶላር በርሜል፣ ለቤንዚን 5.7 ዶላር በበርሜል ነው፡፡ ነዳጅ የማቅረብ ስምምነቱን የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅትን በመወከል ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ታደሰ ኃይለ ማርያም ሲፈርሙ፣ በፔትሮ ቻይና በኩል ደግሞ የኩባንያው ተወካይ ሚኒስትር ደንግ ፈርመዋል፡፡

ከዚሁ ስምምነት ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የአቅርቦትና ሎጅስቲክ ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ችግሮች እያነሳን አንድ በአንድ ለመመልከት እንሞክራለን፡፡

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ከ50 አመት በፊት በመንግስት የተቋቋመ ድርጅት (በተለያየ ግዜ ስያሜው ቢቀያየርም) ሲሆን በተቋቋመበት አላማ መሰረት ለሃገሪቷ የነዳጅ ፍጆታ የሚሆን የትጣራ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባል። በዚሁ አመት 2017 ብቻ ወደ 3.5 ሚሊዮን ቶን ነዳጅ (3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት) ወደ ሃገር ውስጥ ያስገባ ሲሆን በሚቀጥለው አመት 2019 እ.ኤ.አ. ወደ 4.2 ሚሊዮን ቶን ነዳጅ ያስገባል ተብሎ ይገመታል። ይህም ማለት የሃገሪቷ የነዳጅ ፍላጎት በሚቀጥሉት አመታት የ 10% እድገት እያሳየ መሆኑን ነው። ከዚሀ የነዳጅ አቅርቦት ውስጥ 90% ያህሉ ከ ኩዌት አካባቢ ሲሆን የሚያስመጣው፡ የተቀረውን ደግሞ ከሱዳን ነው። በተመሳሳይ 95% ያህል የነዳጅ አቅርቦቱ በጅቡቲ ወደብ በኩል የሚገባ ሲሆን ወደ ሃገር ውስጥ እስከሚጓጓዝ ድረስ እዛው ጅቡቲ በሚገኘው ጅቡቲ ሆራይዘን ነዳጅ ማከማቻ በኪራይ ክፍያ እንዲቀመጥ ይደረጋል።

በአለፈው አመት የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በተመሳሳይ ባወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ ትራፊጉራ የተባለ ድርጅት ያቀረበው የመወዳደሪያ ዋጋ በበርሜል ከ 4 ዶላር በታች ነበር። ይህም ማለት በአንድ አመት ብቻ ወደ 17% የማጓጓዣ ፕሪምየም ጭማሪ አሳይቷል።

የአመት ኮንትራት ለምን መስጠት አስፈለገ?

የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት በየአመቱ ይህንን ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት በየጊዜው መርከብ ቻርተር ከማድረግ ይልቅ የአመት ኮንትራት ለውጭ ድርጅቶች ሀላፊነት ይሰጣል። የመርከብ ቻርተር / ኪራይ በየቀኑ የሚቀያየር ሲሆን እኛ የምናስገባበት የአመት ኮንትራት የተጋነነ ነው። እኛ ነዳጅ ከምናስመጣበት ከኩዌትም ቢሆን እንኳን መርከብ ራሱ ተከራይቶ ቢያስመጣ ኖሮ የማጓጓዣ ወጪው በበርሜል ከ 1 – 2 ዶላር አይበልጥም ነበር። ከ50 አመት በላይ ነዳጅ የማስመጣት ልምድ ያለው ድርጅት የራሱ የሆነ የመርከብ ኪራይ (ቻርተሪንግ ዲፓርትመንት) የሚከታተል አካል አይኖረውም? በአመት የ 3 ቢሊዮን ዶላር የነዳጅ ግዥ የሚፈጽም ድርጅት አይደለም፡ ከዚህ ባነሰ ሁኔታ ግብይት የሚያካሂዱ የውጭ ካምፓኒዎች የራሳቸው ቻርተሪንግ ዲፓርትመንት ኖሮዋቸው መርከብ ተከራይተው ነው ነዳጅ እና መሰል ፔትሮ ኬሚካል ምርቶች የሚያስገቡት። የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ታድያ ለምን ከ 3 እስከ 4 እጥፍ ለመክፈል ፈለገ? የመርከብ ቻርተሪንግ ዲፓርትመንት በቀላሉ ሊኖረው ሲገባ ለምን በየአመቱ አላስፈላጊ ወጭ ይዳረጋል?

ከኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት ጋር በመስማማት መስራት

በቅርቡ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ በኢቲቪ በሰጡት አስተያየት ሁለቱ ነዳጅ ጫኝ መርከቦቻችን ለዚሁ አላማ ተብለው ቢገዙም፡ ከኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ጋር ስምምነት ባለመደረሱ እስከ አሁን መርከቦቹን ለውጭ ድርጅት በኪራይ ተሰጥተው ነው ያሉት። ምንም እንኩዋን የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አንድ ደንበኛን ብቻ ታሳቢ አድርጎ መርከብ መግዛቱ ስህተት ቢሆንም፡ አሁን ግን መርከቦቹ እስከተገዙ ድረስ እና አሁን ባላቸው የነዳጅ መጫን አቅም የሃገሪቷን ፍላጎት ማሟላት እስከቻሉ ድረስ፡ የራሳችንን ነዳጅ ጫኝ መርከቦች መጠቀም ስንችል ለምን ለውጭ ድርጅት ኮንትራት መስጠት አስፈለገ?

አሁን ባለው የነዳጅ አቅርቦት መሰረት በወር የምናስገባው ነዳጅ መጠን ወደ 300 ሺህ ቶን ነው። ሁለቱ የነዳጅ ጫኝ መርከቦች ደግሞ በድምሩ 80 ሺህ ቶን በ አንድ ጊዜ መጫን ይችላሉ። በ አማካይ ከኩዌት ጅቡቲ 5-6 ቀን በሚፈጅ ጉዞ፡ እነዚህ ሁለት መርከቦች አሁን ያለውን አቅርቦት መሽፈን ይችሉ ይሆናል። ከሁለቱ መርከቦች በላይ እንኳን ቢሆን፡የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ባለው ልምድ ተጨማሪ መርከቦች ቻርተር አርጎ አቅርቦቱን ማሟላት ይችላል።

የኢትዮጵያ ንግድ መርከብና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በትብብር ለመስራት፡ እነፈተሽበት ብሎ የድርጅቱን ብቃት ለማሳየት በጠየቅበት ሰአት፡ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አላማው ግልጽ ባልሆነ መንገድ የአንድ አመት ኮንትራት ስምምነቱን ከውጭ ድርጅት ጋር መፈራረሙን መርጧል። የተለየ የጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ለሀገር የጋራ ጥቅም በስምምነት መስራት የስልጥኔ ምልክት ነውና፡ በሚቀጥለው አመት ነገሮች መስመር ይዘው በራሳችን መርከቦች መጠቅም እንደምንችል ተስፋ አለን።

ጅቡቲ ሆራይዘን ነዳጅ ማከማቻ ኪራይ

የኢትዮጵያ ነዳጅ ጅቡቲ ከደረሰ በኋላ ወደ ሃገር ውስጥ ከመግባቱ በፊት በ ጅቡቲ ሆራይዘን ነዳጅ ማከማቻ በጊዜያዊነት ይቀመጣል። ይህም ማለት የተቀመጠው ነዳጅ እስከሚነሳ ድረስ ለነዳጅ ማከማቻው ኪራይ መክፈል ግድ ይላል። ለምሳሌ በአለፈው አመት ለኪራይ የተከፈለው ወደ 2 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ይገመታል። ይህ ኪራይ ክፍያ አሁን ላይ ትንሽ ሊመስል ይችላል። ነገር ግን ከቅርብ አማታት ወዲህ በጅቡቲ ሆራይዘን ነዳጅ ማከማቻ ላይ የሚታየው መጨናነቅ ወደፊት ስጋት ይፈጥራል። ለእመታት ነዳጅ ወደ ሃገር ውስጥ ሲያስገባ የነበረ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅትም ሆነ መንግስት የነዳጅ አቅርቦት ሎጅስቲክ ስትራቴጂው ከዚህ በተሻለ መሆን ይገባዋል። በሰለጠኑት አለም እንደሚታየው በነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዎች በመጠቀም ነዳጅ ጅቡቲ ላይ ሳይቆይ በቀጥታ ከመርከብ ተራግፎ ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ ማድረግ ይቻላል። ምናልባትም ለዚሁ የሚሆኑ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ከጅቡቲ ድንበር በቅርብ ርቀት መገንባት ያስፈልግ ይሆናል። ይህ ነዳጅን በማስተላለፊያ ቧንቧ ማጓጓዝ በአውሮፓ እና በአሜሪካ የተለመደ ነው። ከምጓጓዣ ወጪ አንጻር ሲታይም በእጅጉ ርካሽ እንደሆነ ይነገራል። ከዚሁ ልምድ በመነሳትም ወደፊት የተለያዩ የሃገሪቷን ክፍሎች የሚያገናኙ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧዎችን መዘርጋት ያስፈልግ ይሆናል።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s