የኢትዮጵያ ሎጅስቲክስ ተግዳሮቶች

qwe

Photo credit: ESLSE

ሎጅስቲክስ ለአንድ ሃገር እድገት ወሳኝ እንደሆነ ለሁላችንም ግልጽ ነው። ሎጅስቲክስ የንግድ እንቅስቃሴውን ከማነቃቃት ባለፈ የሃገራችን አስመጭ እና ላኪዎች በአለም ገበያ ላይ ያላቸውን ተወዳዳሪነት በእጅጉ ትጽእኖ ያሳድራል።

የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የኢትዮጵያ የሎጅስቲክስ ዘርፍ አሁን ላይ ያሉት ችግሮች እና እንቅፋቶች የሚወገዱበት ወይም የሚቀንሱበት መንገድ እቅድ ተይዞለት መሰራት ካልተጀመረ፤ በሃገሪቱ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ የበለጠ ፈታኝ ተግዳሮት እንደሚፈጥ ምንም ጥርጥር የለውም።

“The problem is not the problem; the problem is your attitude about the problem.” (ችግሩ ችግሩ አይደለም. ችግሩ ለችግሩ ያለዎት አመለካከት ነው) እንደሚባለው፤ ችግሩ ሃገራችን ያለችበት የሎጅስቲክስ ችግር አለመታወቁ አይደለም። ችግር እንዳለ ከላይ ያሉት የመንግስት አካላትን ጨምሮ እስከ ታች የችግሩ ግፍ ተሸካሚዎች አስመጭና ላኪዎችም ጭምር ይታወቃል። ችግሩ እንደ ሃገር እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ የምናረገው ነገር በአንድም በኩል የረጅም ግዜ እቅድ አለመኖር ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመቅረፍ በባለቤትነት የተወሰነ መንግስት አካል አለመኖሩ ነው።

በ2015 እ.ኤ.አ. Policy Advisory Unit of UNDP Ethiopia የጻፈው Ethiopian National Logistics Strategy 2025 የተባለ ጥናታዊ ሎጅስቲክስ እቅድ አለ። በአሁን ሰኣትም ይሀው እቅድን መሰረት ይደርገ እንቅስቃሴ ነው ያለው። ልብ ብሎ ለተመለከተው በ 2015 የተቀረጸው እቅድ አሁን 2019 ሆነን ስናየው የተራመድነው በጣም ጥቂት እርምጃ ነው፤ እሱም ወደ ኋላ ነው። በ 2014 ወርልድ ባንክ በሚያዘጋጀው አለም አቀፉ Logistics Performance Indicator (LPI) ranking 104ኛ ደረጃ የነበረን ሲሆን፤ በ 2016 ግን ከ 104 ወደ 126 (ከ 160 ሃገራት መካከል) ወርደናል። በተቃራኒው ጎረቤታችን ኬንያ 42 ደረጃ ላይ ናት። ይህ የሚያሳየው እንደ ሃገር እያረግን ያለነው ነገር ብዙም ወደፊት እያስኬደን እንዳልሆነ ነው። በተጨማሪም የ10 አመት ብሄራዊ ሎጅስቲክስ እቅድ የአጭር ግዜ እቅድ ነው። ለግዜው ትንንሽ ችግሮችን ሊፈታ ይችላል፤ ነገር ግን አርቅን እንዳናይ ደግሞ ግርዶሽ ይሆናል። እንደ ሃገር ቢያንስ የ30 አመት እቅድ ይዘን መንቀሳቅስ አለን።

ሌላው ከላይ ለመግለጽ እነደሞከርኩት፤ እንደ ሃገር ያለብንን የሎጅስቲክስ ችግር ለመቅረፍ በባለቤትነት የሚሰራ የመንግስት አካል አለመኖሩ ነው። ሎጅስቲክስ በባህሪው የተወሳሰበ እና ብዙ አካላቶች በአንድነት ተጣምረው የሚሰሩበት ዘርፍ ነው። ከሌሎች በሎጅስቲክስ ዘርፍ ከተሳካላቸው ሃገራት ልምድ እንደምናየው፤ በመንግስት ደርጃ የሃገሪቷን ሎጅስቲክስ እቅድ ለማስፈጸም በበላይነት የሚቆጣጠረው አንድ አካል ብቻ ነው። ወደ እኛ ሃገር ስንመጣ ግን ከፋይናንስ ሚንስትር ጀምሮ፤ ትራንስፖርት ሚንስትር፤ ገቢዎች፤ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን፤ ኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ አገልግሎት ድርጅት (ኢባትሎአድ)ን ና ሌሎችንም መስሪያ ቤቶች ጨምሮ ሁሉም በራሱ መንገድ ችግሮችን ለመቅረፍ ሲጥር ይታያል። በአጭሩ የተማከለ አሰራር የለም። ለዚህም ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በተለያዩ ግዜያት በውጭ አማካሪዎች የምናሰራቸው ጥናቶች ናቸው። በ 2012 ኢባትሎአድ ያሰራው ጥናት፤ በ 2015 እ.ኤ.አ. Policy Advisory Unit of UNDP Ethiopia፤ የፋይናንስ ሚንስትር የሚያሰራው ጥናት፤ ማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን ያሰራው ጥናት፤ ትራንስፖርት ሚንስትር የሚያሰራው ጥናት፤ ወዘተ… ልምድ ያካበቱ የውጭ አማካሪዎችን ቀጥሮ ጥናት ማካሄድ በራሱ መልካም ነገር ነው። ነገር ግን የተለያዩ መስሪያ ቤቶች የራሳቸውን ጥናት የሚያካሂዱ ከሆነ፤ ጥናት ማካሄዱም ብቻም ሳይሆን ሁሉም በራሱ መንገድ ጥናቱን የሚተረጉመው ከሆነ፤ ይህ በራሱ ሌላ ችግር ነው። ለምሳሌ ያህል፤ ኢባትሎአድ በ 2012 ባካሄደው ጥናት መሰረት 2018 ላይ ሲታይ በአብዛኛው ተመሳሳይ ችግሮች ናቸው የሚነሱት። ይህም የሚያሳየው ችግሩ ችግሩን አለማወቅ ሳይሆን፤ ችግሩ ችግሩን ለመፍታት ያለው አካሄድ ነው። ብዙ ጥናቶችም መፍትሄ አያመጣም። ከጥናት በኋላ ያለው የቤት ስራ ሃላፊነት ወስዶ ችግሮችን ለመፍታት የሚንቀሳቀስ አንድ እና አንድ ብቻ የመንግስት አካል መኖር አለበት።

ከሎጅስቲክስ ዘርፉ ጋር በተያያዥነት መነሳት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ። ከዚህ በታች የተወሰኑትን እያነሳን እናያለን።

  1. የአለም ባንክ ድጋፍ

በ2017 የአለም ባንክ የኢትዮጵያን የንግድ ሎጅስቲክስ ዘርፍ ከ 2017-2022 በአምስት አመት ውስጥ ለማዘመን የ 150 ሚልዮን ዶላር ድጋፍ አድርጎ እንቅስቃሴ ተጀምሮ ነበር። ይህ ትልቅ ፕሮጀክት የራሱን መስፈርቶች በግልጽ አስቅምጦ የተጀመረ ነው። ይህ ፕሮጀክት በማሪታይም ጉዳይ ባለስልጣን የበላይ ጠባቂነት መተግበር የሚግባው፡ ከ 1 አመት ከ ግማሽ በኋላ እራሱ አለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት መሰረት ሲገመገም ግን እስከ አሁን ምንም ይህ ነው የተባለ ለውጥ አለመደረጉ ነው። አሁን ባለው ፍጥነት ምናልባትም ከ 3 አመት በኋላ ራሱ የተሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ወይ ሳንጠቀምበት ወይም ገንዘቡ እንዳይመለስ በሚል የይድረስ አይነት የማይረባ ነገር ተሰርቶ ነው የሚባክነው። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት ብዙ መስሪያ ቤቶች የዚህ ፕሮጀክት አስፈጻሚ መሆናቸው ነው። ብዙ አስፈጻሚ ባለበት ሁኔታ ምንም ሊፈጸም አይችልም።

  1. የግል ዘርፍ ተሳትፎ

ሌላው በሎጅስቲክስ ዘርፉ ከሚነሱ ቅሬታዎች አንዱ የግል ዘርፍ (private sector) ያላቸው ድርሻ ነው። በተለይ በመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት በኩል የሚታየውን የአሰራር ጥራት ጉድለት፤ በአንድ የመንግስት ድርጅት በሞኖፖል መያዙ እና ነጻ የሆነ የአገልግሎት ውድድር አለመነሩ ከሚነሱ ተያያዥ ተግዳሮቶች ጥቂቶቹ ናቸው። ምንም እንኳን የዶ/ር አብይ መንግስት የግል አካላትን ድርሻ ለመጨመር እና በዚህ ዘርፍ የጎለበቱ የውጭ ድርጅቶችን ለማሳተፍ የፖሊሲ ለውጥ እንደሚደረግ ቃል ቢገቡም፤ እስከ አሁን ግን ምንም በግልጽ የተቀመጠ መመሪያ ባለመኖሩ የተጠበቀው ለውጥ ሊመጣ አልቻለም። በግል ያነጋገርኳቸውም በሃገራችን ገብተው በሎጅስቲክስ ዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ ፍላጎት ይላቸው ድርጅቶችም ይህንኑ የመንግስት ፖሊሲ ለውጥ እየተጠባበቁ ነው።  ከሌላ ሃገራት ልምድ እንደምናየው መንግስት(ህዝብ) ዘርፍ (public sector) ብቻውን ሁሉንም ነገር ሊሰራ አይችልም። መስራት ቢችልም እንኳን፤ ነፃ ውድድርን ለማበረታታት እና ግልፅነትን/ተጠያቂነትን ለማጎልበት የግል ዘርፍ (private sector) ትሳትፎ መኖር ግድ ይላል። በሃገሪቷ የሚታየውንም የሎጅስቲክስ ዘርፍ የላቀ ደረጃ ላይ ለማድረስ የግል ዘርፍ (private sector) ትሳትፎ መኖር አለበት። የመንግስት የሆነው ኢባትሎአድ እንደ አንድ ተወዳዳሪ ራሱን ሊያቀርብ ይችላል። የግል ዘርፍ መኖሩ ጤናማ ነፃ ውድድር እንዲኖር ያደርጋል። የፈጠራ እና አዳዲስ ግኝቶች በር ይከፍታል። እውቀት እንዲጎለብት በር ይከፍታል።

  1. የኢትዮጵያ መርከቦች

ስለ እኛ ሃገር መርከቦች ሳስብ ሁል ግዜ አይምሮዬ ላይ የሚመጣ ጥያቄ አለ። በአንድ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአለም ላይ የሃገራችንን ስም ከፍ ብሎ እንዲጠራ የሚያደርግ የመንግስት ድርጅት ሲሆን፤ በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ለምን የምናፍርበት ሆን? ሁለቱም የመንግስት ድርጅት ሲሆኑ፤ ከዚህም በዘለለ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት የ FOB Rule ከላላ ያለው ሞኖፖል ድርጅት ሲሆን የድርጅቱ እድገት ወይም ትርፍ ሲታይ ሃገር ውስጥ ካለ ተራ ድርጅት ያነሰ ነው።

እንደ እኔ እይታ የመርከቦቻችንን ችግር በሁለት እከፍለዋለሁ። አንደኛው በኣመራር ደረጃ የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ነፃ ድርጅት አይደለም። መርከብ ድርጅት ነፃ እና ገለልተኛ አመራር እስከለለው ድረስ ከኪሳራ ውጭ የሚያተርፈው ነገር የለም። በሌላ አባባል የመርከብ ድርጅት እንደማንኛውም ቢዝነስ ትርፍ ለማግኘት ነው የሚሰራው። ውሳኔዎች በኮሚቴ ሳይሆን (ያውም ስለመርከብ እውቀት የሌላቸው የ ፖለቲካ ሰዎች) በአንድ ብቃት ያለው አመራር ነው መመራት ያለበት። አሁን እየታየ ያለውም የዚሀ ተቃራኒ ነው። በአሁን ሰአት ድርጅቱን በቀጥታ የሚመሩት ሰዎች ብቃት እና ልምድ ያላቸው ሲሆኑ፤ ነገር ግን አፋጣኝ ውሳኔዎች ወይም መሰረታዊ ለውጦች ከኮሚቴ ውጭ አይከናወኑም። ይህም ለድርጅቱ እድገት የአመታት ማነቆ ነበር፤ ወደፊትም ሆኖ ይቀጥላል።

ሁለተኛ ችግር ብዬ የማነሳው የመርከብ አመራርጣችን ነው። ከ20 አመታት በፊት “General Cargo” ተብለው የሚመደቡ መርከቦች ተመራጭ ነበሩ። የተለያየ እቃ ለመጫን ስለሚያስችሉ፤ በመጠናቸውም አንስተኛ ስለሆኑ፤ እነዚህ መርከብ አይነቶች የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት ምርጫ ነበሩ። ከ አለፉት 20 አመታት በኋላ ግን እነዚህ General Cargo የሚባሉ መርከቦች ጥቅም እየቀዘቀዘ መጥቷል። ምክንያቱም አብዛኛው እቃ በ General Cargo ከመጫን ይልቅ በ ኮንቴይነር “Container Ship” መጫን ስለሚሻል። በኮንቴይነር የማይጫነው እንደ እህል ና ማዳበርያ የመሳሰለው ጅምላ እቃ (Bulk) ደግሞ Bulk carrier ship መጫን ያዋጣል። ነገር ግን እስከ አሁን ድረስ ኢትዮጵያ የምትገዛው የመርከብ አይነት “General Cargo” የሚባሉትን ነው።  በሚያሳዝን ሁኔታ በ General Cargo መርከብ በተከታታይ ጅምላ እቃ (Bulk) የምንጭን ከሆነ ስለ መርከብ ገና ብዙ ያልገባን ነገር አለ ማለት ነው። እንደ መርከብ ድርጅት ወደ ሃገር ውስጥ ለሚቀጥሉት 20-30 አመታት የሚገባውን እና የሚወጣውን የእቃ አይነት ላይ የተመሰረተ የገበያ ጥናት በማድረግ ያሉንን የመርከብ አይነቶች የተወሰኑትን Bulk carrier ship፤ የተወሰኑትን Container Ship፤ የተወሰኑትን ደግሞ General Cargo አይነት አርጎ ለሁሉም የገበያ ሁኔታ ማዘጋጀት ሲገባ፤ ነገር ግን አሁንም ስለ መርከብ ምርጫችን ችግር የተረዳን አይመስለኝም።

  1. የባህር ወደብ አጠቃቀም

ስለባህር ወደብ አጠቃቀም ከዚህ በፊት ያነሳሁት ነገር ነበር። በተለይ ስለ ኤርትራ ወደብ አጠቃቀም በተለይ አሁን ስምምነቶች መስመር በሚይዙበት ሰአት በጥንቃቄ ማየት ያለብን ጉዳዮች አሉ። ከልምድ እንዳየነው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ከአሰብ እና ምፅዋ ስንለቅ እና ፊታችንን ወደ ጅቡቲ ስናዞር የዘነጋነው ነገር፤ ነገር ግን በኋላ ብዙ ዋጋ ያስከፈለን ነገር ነበር። በወቅቱ ጅቡቲን ወደብ ለማየት እድሉ የነበረን ሰዎች እንደምናስታውሰው፤ ጅቡቲ በዛን ሰአት ወደብ ለመባል ራሱ የሚያበቃ ደረጃ ላይ ሳትሆን ነበር የኢትዮጵያ መርከቦችን ጨምሮ የገቢ ወጪ እቃ በጅቡቲ ወደብ እንዲሆን የተወሰነው። እቃ ከመርከብ ለማወርድ እንኳን የሚበቃ መሳራያ ባለመኖሩ ከየመርከቦቹ ላይ እየተወጣጣ ነበር ለጅቡቲ ወዛደሮች የሰጠነው። አሁን የምናያት ጅቡቲ የተገነባችው በኢትዮጵያ ገንዘብ ነው። እገር ግን ያኔ መጀመርያ ወደ ጅብቲ ስንሄድ መንግስት ከጅቡቲ ጋር ተደራድሮ የ ኢትዮጵያን ዘላቂ ጥቅም ለረዥም አመታት የሚያስከብር ስምምነት ማድረግ ነበረበት። ያኔ የመደራደር ሃይል (bargaining power) የነበረው ከኢትዮጵያ ጋር ነበር። አሁን ግዜው ካለፈ በኋላ ነው በ ዶ/ር አብይ ዘመን ትዝ ብሎን ከጅቡቲ ጋር ለመደራደር እና የተወሰን የወደብ ድርሻ ለመያዝ የምንጥረው። በርበራም ላይ እንደዚሁ። አሁንም ከ ኤርትራ ጋር በምናረገው የወደብ አጠቃቀም ድርድር ያለንን የመደራደር ሃይል (bargaining power) ተጠቅመን ዘላቂ ነገር መያዝ አለብን። ለምሳሌ የትወሰነ የወደቡን ቦታ በ 50 አመት የሚታደስ ኪራይ ከኤርትራ መውሰድ። የራሳችን የወድብ ቦታ ካለን ከቦታ ሊዝ ኪራይ ውጭ የምንከፍለው አይኖርም። ነገር ግን እንደ ወደብ ባለቤት የ ወደብ ክፍያ ራሳችን መቆጣጠር እንችላለን። በተጨማራም ከራሳችን ወደብ በቀጥታ እቃ መኪና ወይም ባቡር ላይ ተጭኖ ያለ ኤርትራ ፍተሻ ወደ ሃገር ውስጥ ማስገባት ይቻላል።

ከላይ የጠቀስኳቸው የራሴን አመለካከቶች ነው። የፅሁፌም አላማ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን ችግር ለመንቅፍ ሳይሆን፤ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ያሉት ችግሮች በሎጅሲክስ ዘርፉ ላይ ያላቸውን አሉታዊ ተፅእኖ አጉልቶ ለማሳየት ነው። በመንግስትም የሚደረጉ ውሳኔዎች የረጅም ግዜ እይታ እንዲኖራቸው ለመጠቆም ነው። እንደ ሁል ግዜው አስተያየቶችን ለመቀበል ዝግጁ ነኝ።

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s