የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ 2011 – 2020 በእኔ እይታ

አዲሱን የሃገራችንን ብሄራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ 2011 – 2020 (National Logistics Strategy 2018 – 2028) ከቀናት በፊት የትራንስፖርት ሚኒስትርና የማሪታይም ጉዳዮች ባለስልጣናት ባሉበት በሸራተን ሆቴል ”ለባለድርሻ አካላት” ይፋ ሆኗል። ይህ ባለ100 ገጽ ሰነድ እጄ ላይ ስለገባ በጥሞና ካነበብኩት በኋላ የራሴን እይታ እንደሚከተለው አስፍሬያለሁ።

ብሄራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ለምን አስፈለገ?

በአጭሩ የሃገራችን እድገት ማነቆ ከሆኑበት ነገሮች አንዱ ሎጅስቲክስ ስልሆነ። ይህን ለማወቅ ብዙ ርቅት መጓዝ አያስፈልግም። የወጭ ገቢ እቃዎችን ብቻ መመልከት በቂ ነው። ይህን ዘርፈ ብዙ የሎጅስቲክስ ችግሮች ለመቅረፍ ብዙ ጥረቶች ቢደረጉም፣ በሃገር ደረጃ ብሄራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ሲነደፍ የመጀመሪያው ነው። በብሄራዊ ደረጃ መዘጋጀቱም ከዚህ በፊት በተከፋፈለ መንገድ ሲደረጉ የነበሩ እርስ በርስ የማይናበቡ አሰራሮችንና መፍትሄዎችን ያስቀራል።

ብሄራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ውጥን ሃሳብ መቼ ተጀመረ?

ብሄራዊ ይሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ለመቅረጽ የተጀመረው አሁን አይደለም። የቅርብ ግዜውን ለማስታወስ እንኳን በ 2014 (እኤአ) በ UNDP እርዳታና NATHAN ASSOCIATES በተባለ ድርጅት የተሰራው ጥናትን ማንሳት ይቻላል። በ 2017 ም እራሱ UNDP ያሳተመው በኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄ መሰረት የተዘጋጀ ‘’National Logistics Strategy’’ የሚል ጽሁፍም በዚህ ተርታ የሚመደብ ነው። የዚህን ጥናትን እንዲሁም የራሳቸውን ሃሳብ መሰረት ያደሩጉ ብሄራዊ መልክ የተላበሱ ነገር ግን ስራ ላይ ያልዋሉ ሌሎች ስትራቴጂዎችም ተሰራጭተዋል። ስለዚህም ይህን ከአምስት አመታት በላይ ሲንከባለል የመጣን ስትራቴጂ አሁን እንደተፈጠረ አርገው፤ ራሳቸውን በራሳቸው እጅ ጀርባቸውን እየመቱ የሚያደንቁ ሰዎች የብዙ ሰዎች ድካም ውጤት እንደሆነ እንዲገነዘቡት ይገባል።

ይህ ብሄራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ በጥቅሉ ሲታይ ብዙ መልካም እይታዎችን የያዘና የሃገሪቷን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃ ሙሉ እምነት አለኝ። በዚህም ፕሮጀክት ላይ የተሳተፉና ወደ ተጭባጭ ስትራቴጂ ለቀየሩት ሰዎች ምስጋናዬንና አድናቆቴን ለመግለጽ እወዳለሁ። የጽሁፌ መነሻ ግን ያሉትን በጎ ጎኖች እያደነቁ ለማሞገስ ሳይሆን፣ በእኔ እይታ የጎደሉትን ነገሮች በስሱ ለመዳሰስ ነው። እነዚህ ከዚህ በታች የማነሳቸው ነጥቦች ምናልባትም የአሁኑ ስትራቴጂ በሚከልስበት ጊዜ እንደ ግብአት ሊያገልሉ ይችላሉ።

የስትራቴጂው ተደራሽነት ጥያቄ፣

በቅርቡ ለመመረቂያ ጽሁፌ ግብአት እንዲሆን ስለ ሃገራችን ሎጅስቲከስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመጠይቅ መራጃዎችን ሰብስቤ ነበር። አለም ባንክ ራሱ የሚጠቀምበትን መጠይቅ ነበር የተጠቀምኩት። ከታች በምስሉ እንደሚታየው የሎጅስቲክስን ለውጥ በተመለከተ የሚደረጉ የህግ ወይም የፖሊሲ ለውጦች እታች እንደማይወርዱ ነው። ይባስም በአለፉት 5 አመታት የህግ ወይም የፖሊሲ ለውጥ ወደታች ተደራሽነታቸው ተባብሶበታል። ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ አንዱ የሎጅስቲክስ ድርጅት ቢሮ ገብቶ መጠየቅ ነው። መንግስት የሚከተለው አሰራርም ሆነ እቅድ ከብዙዎቹ ባለድርሻ አካላት የተሰወረ ነው። በ EMAA (ማሪታይም ጉዳዮች) ወይም ERCA (ገቢዎችና ጉምሩክ) ድሀረ ገጽ ላይም መመልከት ይቻላል። መራጃዎች ወደሚመለከታቸው አካላቶች አይደርስም። ይህ ባለበት ሁኔታ በብሄራዊ ደራጃ ሁሉን ያሳተፈና ያናበበ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ መተግበር ቀላል አይደለም።

ስድፍ

ሌላው ከላይ ባለው ምስል ላይ እንደምናየው በጉምሩክ በኩል ሊደነቅ የሚገባ የተመሰከረለት ለውጥ መኖሩን ነው። አብዛኛው ሰው ጉምሩክን ከመጥፎ አሰራር ጋር የሚያመሳስለው ነገር አለ። ሎጅስቲክስን በተመለከተ ግን አለም ባንክ ራሱ ባስቀመጠው መስፈርት ከሌሎቹ ስድስት ምስፈርቶች አገራችን ጥሩ ነገር ያስመዘገበችው በ ጉምሩክ በኩል ነው። አሁን ጎልተው የሚታዩት የጉምሩክ እንከኖች ከአሁን በተሻለ ቴክኖሎጅን ባለመጠቀምና መልካም አስተዳደር ላይ ባለመሰራቱ እንጅ ከዚህም በላቀ ሁኔታ የሚጠበቅበትን ድርሻ ለመወጣት የሚችል የመንግስት ድርጅት ነው።

በአለም ባንክና በ ናታን አሶሲየት መረጃ ላይ የተመረኮዘ ስትራቴጂ፣

አሁን ይሁንታን አግኝቶ የጸድቀው ብሄራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ 2011 – 2020 መሰረቱን በ Nathan Associates ጥናትና World Bank Logistics Performance Index ላይ እንዳደረገ ተገልጿል። በናታን የተሰራው ጥናት ከአምስት አመት በላይ ሆኖታል። የአለም ባንክም LPI ከመረጃ በዘለለ ለእንደ ኢትዮጵያ ላሉ ወደብ-አልባ ሃገራት ያለው ዋጋ ጥያቄ ውስጥ መግባት ከጀመረ ከረመ። ይልቁንም ሃገራችን የራሷን ጥናት አካሂዳ፣ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት (stakeholders) አማክራ መሆን ነበረበት። የተወሰኑ ጥናቶች መደረጋቸውን፣ የጥናት ውጤቶቹ ጭምር እጄ ላይ አለ። ግን እነዚህና መሰል ጥናቶች ውጤት በሎጅስቲክስ ስትራቴጂው ውስጥ አልተካተቱም። ለምሳሌ ያህልም የመንግዶቻችን ዲዛይን፣ የጭነት መኪናዎች axle load መንገዶቻችን ላይ እያደረሰ ያለውን ውድመት፣ በባቡር አገልግሎት ላይ የሚታዩትን ችግሮች እና ሌሎችንም ማንሳት ይቻላል። የአለም ባንክ የሎጅስቲክስ ደረጃ ምደባ የተዛባና ትክክለኛውን ዘገባ እንደማይሰጥ በመረጃ የተደገፈ ክርክርም ማንሳት ይቻላል። ለምሳሌ በ2016 እና በ2108 የኢትዮጵያ የ Domestic LPI ሪፖርት ምንም ሳይቀየር ነው የቀረበው። አለም ባንክ ትክክለኛ መረጃ ላይ መሰረት ያደረገ ሪፖርት ቢያቀርብ ኖሮ በኢትዮጵያ የተመዘገበውን ለውጥ በሪፖርቱ ላይ ማየት ይቻል ነበር።

International or Domestic LPI?

ሌላው በብዥታ ተምታቶ የተገለጸው ነገር በአንድ በኩል የአለም ባንክ የ International LPI መሰረት ያደረገ ገለጻ ሲደረግ፣ የተዘነጋው ነገር እንደ እኛ ላለ ወደብ አልባ ሃገር ከ International LPI ይልቅ የ Domestic LPI ሪፖርት ላይ ትኩረት አለመደረጉ ነው። ምክንያቱም በ የ International LPI ላይ ደረጃው መሰርት የሚያረግው በሃገራችን ሳይሆን በጎረቤት በምንጠቀማቸው transit countries ነው። እነዚህ ሃገሮች፣ ጅቡቲ ሱዳን ሱማሊያ ና ኬንያ፣ ያላቸው የአማካይ የሎጅስቲክስ ብቃት ነው እንደ እኛ ሃገር ተደርጎ የሚቆጠረው። ስለዚህም ስለኢትዮጵያ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ስናወራ ወይም ስናቅድ የሚያመዝነው የቤትስራ ያለው Domestic ላይ ነው። የራሳችን ወደብ እስከሌለን ድረስ ድንበር አቋራጭ የንግድ ዝውውር ብቃትን ማሳደግ የሚቻለው ከጎረቤት ሃገሮች ጋር በሚደረግ የጋራ ስምምነትና ትብብር ብቻ ነው። ይህ ሃሳብ ወደሚቀጠለው አንገብጋቢና ወሳኝ ነጥብ፣ ግን በሎጅስቲክስ ስትራቴጂው ላይ ያልተገለጸውን ነጥብ እንዳነሳ ያስገድደኛል።

ባለ ድርሻ አካላት – ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ የት ገቡ? ነጋዴዎችስ የት ገቡ?

በብሄራዊ የሎጅስቲክስ ስትራቴጂ 2011 – 2020 ላይ ባለድርሻ አካላት ተብለው ከተገለጹት ውስጥ በሚያሳፍር ሁኔታ ጎረቤት ሃገራት፣ ያውም ወደባቸውን የምንጠቀመው፣ እነ ጅቡቲ ሱዳን ሶማሊያ ኬንያ እንደባለድርሻ አካላት አልተገለጹም። ገጽ 8 ላይ ‘Foreign Affairs and National Security Policy and Strategy’’ በሚል ርዕስ ስር ከመጠቀስ በዘለለ የነዚህ ሃገራት በሃገራችን ሎጅስቲክስ ላይ ያላቸው ሚና የሚገባውን ዝርዝር ይዞ አልተገለጸም። ይባስም ‘’4.2 The role of stakeholders’’ ከገንዘብ መዋጮ ውጭ ምንም የማይጠቅሙን ሁሉ ሲዘረዘሩ እነዚህ ጎረቤት ሃገራት አንዳቸውም አልተጠሩም። ባጭሩ ጎረቤት ሃገራትን ባለድርሻ አካላት ያላደረገ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂ ሙሉ ነው ለማለት አያስደፍርም። በተለይም ደግሞ በ customs, international shipments, tracking and tracing, timeliness በመሳሰሉ የሎጅስቲክስ ብቃት አመላካች ዘውጎች ላይ የራስምታት የሆኑብን መሰረታዊ ተግዳሮቶች ያሉት እንዚህ ሃገራት እጅ ውስጥ እንደሆነ ስናውቅ፣ በግዜ እነዚሀን ጎረቤት ሃገራት ባለድርሻ አካላት አርገን እንድንመለካታቸው እንገደዳለን።

እድገትና ትራንስፎርሜሽን 2 – የሃሳብ መተላለፍ

ገጽ 9 1.1.5 Growth and Transformation Plan II (GTP II) (2015/16-2019/20) በሚለው አንቀጽ ስር የተጻፈው ደግሞ መነበብ ያለበት ይመስለኛል። ሙሉ ጽሁፉን ወደጎን በመተው GTP II ን በቅጡ ካለመረዳት የተነሳ ግብርና እንደዋና የእድገት ዘዋሪ ተደርጎ በጥራዝ ነጥቅ የተወሰድው ስህተት ነው። ምክናያቱም በ GTP II ከግብርና ላይ መሰርት ካደረገ ኢኮኖሚ ወደ ቀላል እንዱስትሪ መሸጋገሪያ የተነሳው አንኳር ነገር ተዘሏል። ብሄራዊ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂውም ይህኑ እውነታ የዘለለው ይመስለኛል። በ GTP II መርህ መሰረት እየተገነቡ ያሉትም ወደፊት የሚገነቡትም ኢንዱስትሪ ፓርኮች የዚህ አካል ናቸው። ሎጅስቲክስ ስትራቴጂውም እነዚህን ኢንዱስትሪ ፓርኮች በስሱ ሁለት ጊዜ ብቻ ጠቅሷቸው የሚያልፈው።

ወደብ አልባ ሃገር ከነጀርመን ጋር ማወዳደር ና የተዛቡ መረጃዎች፣

በ National Logistics Strategy 2018 – 2028 ውስጥ የተጠቀሱ ያማነጻጸሪያ ሰንጠርዦች አሉ። ማነጻጸሩ ባልከፋ፣ ግን ኢትዮጵያን ከማን ጋር ነው የምናወደድረው? አንደኛ የሃገሪቱን geographical disadvantage (being land-locked country) የረሳ ያስመስለዋል። ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት International LPI እንደመረጃ ወስዶ ንጽጽር ውስጥ መግባት የአለም ባንክን መረጃ ምንም እንዳለመረዳት ነው። ለምሳሌ ከላይ የገለጽኩትን መረጃ በተዛባ መንገድ ወስዶ Ethiopia is one of the lowest performing countries in trade logistics i.e., 126th out of 160 countries in LPI rank የሚል የተሳሳተ ድምዳሜ በገጽ 16 ላይ ሰፍሯል። ሌላ የተሳሳተ ድምዳሜ While the logistics performance of many countries has shown improvement, Ethiopia’s performance has deteriorated on the contrast በዚሁ ገጽ ላይ። ይህንና የመሳሰሉ የተዛቡ ድምዳሜዎች በዚሁ ሰነዶች ላይ በብዛት ይታያል። ሌሎች ያዘጋጁልንን መረጃ እንደወረደ መውሰድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በዚህ ሃገራዊ ሰነድ ላይ መታየት የነበረበት በራሳችን ዜጎች የተሰራ ጥናት ውጤቶች ቢሆኑ ጥሩ ነበር።

ቆየት ያሉ መርጃዎች፣

በዚሁ National Logistics Strategy 2018 – 2028 ሌላው የምናስተውለው ነገር አንዳንድ መረጃዎች የቆዩና በአሁን ሰአት ያለውን እውነታ የማይገልጹ መሆናችው ነው። ለምሳሌ ገጽ 28 ላይ ያለው ስለምስራቅ አፍሪካ ትራንስፖርት የሚያወዳድረው ከ5 አመት በፊት የተደረገን ጥናት መሰረት ያደረገ ነው። ከ 5 አመታት በኋላ ቢያንስ የተወሰኑት ሃገራት የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ጀምረዋል። ይህ ግምት ውስጥ ሲገባ የቀረበው መረጃ አብላጫው አሁን ላይ ተቀባይነት አይኖረውም።

አረንጓዴ ሎጅስቲክስ (Green Logistics)

ሌላው በዚሁ ሰነድ ላይ የተገለጸው ስለ አረንጓዴ ሎጅስቲክስ (Green Logistics) ነው። ይህም አሁን ከአለው የአካባቢ ብክለት መከላከል ጋር ጥሩ ሃሳብ ቢሆንም ስትራቴጂው ብስሱ ጨረፍ አርጎ ያለፈውና ትኩረት ያልተሰጠው ዕርስ ነው። ለምሳሌ በግጽ 78 ላይ Transform Modjo Dry Port to green logistics hub ይልና እንዴት ይህ እንደሚተገበር ሳይገልጽ ያልፋል። ሌላም ቦታ ላይ አረንጓዴ ሎጅስቲክስ (Green Logistics) በምን እንደሚለካ ራሱ የተገለጸ ነገር የለም። አረንጓዴ ሎጅስቲክስ (Green Logistics) ከሚያቀርባቸው መፍትሄዎች አንዱ modal shift ነው። የጭነት መኪናዎች የሚያደርሱትን ከመጠን ያለፈ አካባቢ ብክለት ለመቀነስ ከመኪና ትራንስፖርት ወደ ባቡር መቀየር አንዱ ነው። ይህም modal shift ይባላል። ባቡር ኤሌክትሪክ ሰለሚጠቀም፣ ባንድ ግዜ ብዙ እቃም ማጓጓዝ ስለሚችል አረንጓዴ ሎጅስቲክስ (Green Logistics) ለማሳካት ጥሩ አማራጭ ነው። በ ሎጅስቲክስ ስትራቴጂው ውስጥ modal shift ቦታም አልተሰጠው፣ ስለሚችል አረንጓዴ ሎጅስቲክስ (Green Logistics) በምን እንደሚሳካ ጭብጥ የሚለካ ምስፈርት አልቀረበም።

ጊዜ ገደብና የስኬት መስፈርት፣

ሌላው በጉልህ የሚታየው ነገር ለቀረቡት Interventions (መፍትሄ ሃሳቦች – if I am translating it correctly) ብለው ለቀረቡት የግዜ ገደብ አለመቀመጡ ነው። የተወሰኑት የግዜ ገደብ ሲኖራቸው አብዛኛው ግን ብጥቅል የተቀመጠና ግዜ ገደብ የልተያዘላችው ናቸው። በተጨማሪም የስኬት መስፈርት ምን እንደሆነ የተገለጸ ነገር የለም። ለምሳሌ ያህል Establish E-commerce system to minimize logistics cost and time (ገጽ 70) የሚል Interventions መቼ ነው የሚሳካው? መሳካቱስ የሚለካው በምንድነው? ለማሳካትስ የቀረበ standard ምንድነው? ይህ ና መሰል ጥያቄዎች በአግባቡ አለመመለስ ወደፊት ለሚመጣ ተጠያቂነት ቀዳዳ ከፋቾች ናቸው። ስትራቴጂ በትንሹ ሊያሟላቸው የሚገባ መስፈርቶች (Specific, Measurable, Achievable, Realistic and Time-bound) የሚባሉት ሲሆን በ National Logistics Strategy 2018 – 2028 የቀረቡት Interventions (መፍትሄ ሃሳቦች) አብላጫው እነዚህን መስፈርቶች አያሟሉም። የተዘረዘሩት Interventions – achievable ናቸው? በ 2020 የምናየው ነው።

ለማጠቃለል ያህል National Logistics Strategy 2018 – 2028 የሃገራችንን የሎጅስቲክስ ተግዳሮቶች በተወሰነ መልክ እንደሚቀርፍ ምንም ጥርጥር የለውም። የመጀመሪያም ስትራቴጂ እንደመሆኑ መጠን ከላይ የተዘረዘሩትና ሌሎች ክፍተቶች የሚጠበቁ ናቸው። ለዚህ ስትራቴጂ መሳካት መንግስት ብቻውን የሚያመጣው ተአምር የለም። ሁሉም ባለድርሻ አካላት የአቅማቸውን መሳትፍና ያባለቤትነት ሃላፊነት መውሰድ አለባቸው። ባለድርሻ አካላትም በአግባቡ ተለይተው ይህንኑ ሃላፊነት እንዲጋሩ መደርግ አለበት።

2 Comments

Leave a comment